ታሪክ
ሁሉም የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1971 ዴሪክ ፕሪንስ በፎርት ሎደርዴል፣ፍሎሪዳ በሚገኘው ቤቱ በነበረው ጋራዥ ውስጥ ቢሮ ሲከፍት ነበር። መጀመሪያ ላይ የዴሪክ ፕሪንስ ህትመቶች በመባል የሚታወቀው፣ እ.ኤ.አ በ1944 ጌታ በሚከተለው መንገድ በተናገረው ጊዜ የተጀመረው የዴሪክ የበለጸገ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አገልግሎት ውጤት ነበር።
"በእውነትና በእምነት እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ ፍቅር፣ለብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እንድትሆን ተጠርተሃል።"
እነዚህ ቃላት የዴሪክን በመንፈሳዊ ነገር የተራቡትን የመመገብ ጥረት አቀጣጠሉት፣ “ሰልፍ-ስተዲ ባይብል ኮርስ” (እ.ኤ.አ 1969)፣ “ሊበሬቲንግ ትሩዝ” (እ.ኤ.አ 1966)፣ “ሪፔንት ኤንድ ቢሊቭ” (እ.ኤ.አ 1966) እና ሌሎችንም ጨምሮ የተለያዩ መጻሕፍትን እንዲጽፍና ራሱ እንዲያሳትም አነሳሱት። የእነዚህ መጻሕፍት ስኬትና የእግዚአብሔር ታማኝነት ማረጋገጫ እንደመሆኑ መጠን የዴሪክ ፕሪንስ ህትመቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው ፍላጎት አደጉ።
እ.ኤ.አ በ1972 ብቻውን ያዘጋጅ የነበረው ሥራ ከዴሪክ አቅም በላይ ሆኖ እያደገ ስለመጣ፣ ዴቪድ ሴልቢ (አማቹ) እንዲረዳው ተጋበዘ። አብረውም እያደገ ለመጣው አገልግሎት የሬዲዮ ስርጭትን በመጀመርና አዳዲስ መጻሕፍትን በማሳተም አቅጣጫ አስቀመጡ።
እ.ኤ.እ በ1980ዎቹ በኒውዚላንድ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ፣ በእንግሊዝ እና በኔዘርላንድስ የውጭ ቢሮዎች ተከፍተው ሕዝቦችን በደቀ መዝሙርነት የማስተማር ሕልሙ እውን ሆነ። በአሥር ዓመቱ መጨረሻ ዴሪክ ሦስት ጊዜ ዓለምን በመዞር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን ሰጥቷል፣ የሬዲዮ ፕሮግራማቸውም በስድስት አህጉራት እና በአሥር ቋንቋዎች በስፋት ተሰራጭቷል።
እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም. የዴሪክ ፕሪንስ ህትመት በይፋ ወደ ዴሪክ ፕሪንስ ሚኒስትሪስ ተቀየረ። የነጻ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቁሳቁሶች ስርጭት ተጠናክሮ በአጠቃላይ 140 አገሮችን የደረሰ ሲሆን የዴሪክ መጻሕፍትም ከ50 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉመው ይገኛሉ።
ዴሪክ ፕሪንስ ሚኒስትሪስ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ከ45 በላይ በሆኑ አገራት ቢሮዎች ያሉት ሲሆን በየሃገሩ፣ በየባህሉና በየቋንቋው የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለማስተማር በሙሉ ልቡ ቁርጠኛ ሆኖ ቀጥሏል። የአገልግሎቱ እድገትና ስኬት ጌታ እ.ኤ.አ በ1941 ለዴሪክ የተናገረውን ትንቢታዊ ቃል ያረጋግጣል፤ በዚያን ጊዜ ጌታ እንዲህ ብሎታል፦
እንደ ትንሽ ጅረት ይሆናል። ጅረቱም ወንዝ ይሆናል። ወንዙም ትልቅ ወንዝ ይሆናል። ትልቁ ወንዝም ባሕር ይሆናል። ባሕሩም ታላቅ ውቅያኖስ ይሆናል፥ ይህም በአንተ በኩል ይሆናል፤ ነገር ግን እንዴት እንደሚሆን ማወቅ የለብህም፥ ማወቅም አትችልም፥ ልታውቅም አይገባህም።
እግዚአብሔር ለዚህ ቃል ያለው ታማኝነት የዴሪክ ፕሪንስ ሚኒስትሪስን ዛሬ ላለበት ደረጃ ያደረሰው ሲሆን ወደፊትም አገልግሎቱን ወደ “ታላቅ ውቅያኖስ” ማሳደጉን የሚቀጥል ይሆናል።
በደሬክ ፕሪንስ የተዘጋጁ በርካታ የጽሑፍ፣ የድምጽ እና የምስል መረጃዎችን በመጠቀም፣ አገልግሎቱ አዳዲስ መጻሕፍትን ማሳተም ቀጥሏል። እስከዛሬ ድረስ ከ100 በላይ መጻሕፍት ታትመው ከ100 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል።