ዴሪክ ፕሪንስ ነኝ፤ ከቃሉ ለእናንተ የሚሆን መልዕክት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ።

እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፤እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ። ከሚከብቡኝ ከአእላፍ ሕዝብ አልፈራም። መዝሙር 3:5-6

ለእንቅልፍ ማጣት መድኃኒት አለ። በየምሽቱ ጸጥ ያለ፣የተባረከ እና ኃይልን የሚያድስ እንቅልፍ የማግኘት እርግጠኝነት ምን ማለት እንደሆነ ከእናንተ መካከል ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ ብዬ አስባለሁ። በዚህ በዘመናዊው ሥልጣኔያችን ውስጥ በእንቅልፍ ማጣት የሚሰቃዩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ማን ሊቆጥር ይችላል? ነገር ግን መድኃኒቱን ያገኘ አንድ ሰው አለ፦ እተኛለሁ፣አንቀላፋለሁም፤ጌታ ደግፎኛልና ነቃሁ፤ይላል። ያ ሰው እናንተ ያለባችሁ ዓይነት ጫና እንዳልነበረበት ታስቡ ይሆናል። ለነዚህ ሁሉ ፈተናዎች አልተጋለጠም፣ጭንቀትና ሐሳብም አልነበረውም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ነገር ግን በጣም ተሳስታችኋል። እርሱ ምናልባት በእናንተ ሕይወት ውስጥ ካጋጠሟችሁ በላይ ብዙ ጠላቶች፣ከፍተኛ ጫናዎች እና አደገኛ ሁኔታዎች ተጋርጠውበት ነበር። ነገር ግን እርሱ ምስጢሩን አግኝቶ ነበር።

እተኛለሁ፣ አንቀላፋለሁም፤ ደግሞም እነቃለሁ፤ አልፈራም። ለምን? ጌታ ስለሚደግፈኝ ነው። በየሌሊቱ ራሱን ለጌታ አሳልፎ ይሰጥ ነበር። በጌታ ላይ ባለው መተማመን ይተኛ ነበር። ነፍሱ በጌታ ጥበቃ ስር ደህንነቷ የተጠበቀ መሆኑን ያውቅ ነበር። ያለ ጭንቀት፣ያለ ፍርሃት፣ያለ እንቅልፍ ማጣት ስቃይ መተኛትና መንቃት ይችል ነበር። በዚያ አስከፊ የእንቅልፍ ማጣት ስቃይ የምትሰቃዩ ከሆነ፣የዳዊትን ቃላት አስታውሱና ተግብሯቸው።