የእርዳታ ጥሪ

ዴሪክ ፕሪንስ
Published: 1970
Last Updated: ኦክቶበር 2026
Read Time: 2
እግዚአብሔር የመጨረሻ ሐኪማችሁ እና የእውነተኛ ፈውስ ሁሉ ምንጭ መሆኑን እወቁ። ለእርዳታ ወደ ጌታ ጩኹ፤ጸሎታችሁንም እንደሚሰማ በሙሉ ልብ እመኑ።
ዴሪክ ፕሪንስ ነኝ፤ ከቃሉ ለእናንተ የሚሆን መልዕክት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ።
አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ ምሕረትም አደረግህልኝ። መዝሙር 30:2
መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ከሚባርኩኝ ነገሮች አንዱ ጥልቅ የሆነው ቀለል ያለ አገላለጹ ነው። በጣም ጥልቅ የሆኑ እውነቶችን በቀላልና አጠር ባሉ ቃላት ይገልጻል። አሁን ያቀረብኩላችሁን ያንን ጥቅስ ስመለከት የሚገርመኝ ነገር፣ በውስጡ ያሉት ቃላት ሁሉ እጅግ አጫጭር መሆናቸው ነው። “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ወደ አንተ ጮኽሁ አንተም ፈወስኸኝ።” በእነዚያ ቀላልና አጫጭር ቃላት ውስጥ ምንኛ ታላቅ እውነት ተገልጦአል!
እግዚአብሔር የሕዝቡ ፈዋሽ መሆኑን ተገንዝባችሁ ይሆን ብዬ አስባለሁ? ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው ዘጸአት ውስጥ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝ”፤ እኔ ጌታህ፣ሐኪምህ ነኝ። በአዲስ ኪዳንም በያዕቆብ በመልእክት ውስጥ፤ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተጽፏል፦ “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለን? የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በእርሱም ላይ ይጸልዩ፣በጌታም ስም ዘይት ይቀቡት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል።” ጌታ በደስታ እርፍት ሊሰጣችሁ የሚፈልገውን ማንኛውንም ዓይነት ሕመም፣አካላዊ ጭቆና ወይም ሸክም ተሸክማችሁ ይሆን? ወደ ጌታ ለመጮኽ አስባችሁ ታውቃላችሁን? የእነዚህን ቃላት ቀላልነት አስተውሉ፦ “ወደ አንተ ጮኽሁ፣አንተም ፈወስኸኝ።”
ይህንን ምክር እንድመክራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን? ስለ ሐኪሞች፣ስለ ነርሶች እንዲሁም የታመሙትንና የደከሙትን ለሚረዱ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደማመሰግን መናገር እወዳለሁ። ነገር ግን ዋነኛው ፈዋሽ እግዚአብሔር ነው። ታዲያ ጉዳያችሁን ወደ እርሱ ለምን አታቀርቡም? እኔ ይህንን ብዙ ጊዜ አድርጌዋለሁ፣ እርሱም ፈውሶኛል። ለእናንተም እንደሚያደርግላችሁ አምናለሁ።

ኮድ: WD-WFTW-031-AMH









