ዴሪክ ፕሪንስ ነኝ፤ከቃሉ ለእናንተ የሚሆን መልዕክት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ።

ኢየሩሳሌምስ እርስ በርስዋ እንደ ተገጠገጠች ከተማ ተሠርታለች። የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ ዘንድ፥ ለእስራኤል ምስክር ሊሆኑ የእግዚአብሔር ነገዶች ወደዚያ ይወጣሉ። መዝሙር 122:3–4

እግዚአብሔር ሕዝቡ የእርሱ ሕዝብ መሆናቸውን ለዓለም ሁሉ ምስክርነት እንዲሰጡ ያሰበው በዚህ መንገድ ነው። ለእግዚአብሔር ስም ምስጋና ለማቅረብ አብረው እንደሚወጡ ይናገራል።

በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ እግዚአብሔር ስሙን ያኖረበትን አንዲት ስፍራ በእስራኤል ውስጥ ለየ፣ እሷም የኢየሩሳሌም ከተማ ነበረች፤ እንዲሁም በየዓመቱ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ከተወሰነ ዕድሜ በላይ የሆኑ ወንድ እስራኤላውያን ሁሉ ወደዚያ ስፍራ እንዲወጡ፣ከየነገዱና ከየአገሩ ካሉ ወገኖቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ እንዲሁም በአንድነት ሆነው ለእግዚአብሔር ስም እንዲሰግዱና ምስጋና እንዲያቀርቡ አዘዘ። ይህም በዙሪያቸው ላሉ አሕዛብ ሁሉ፣እነርሱ የአንድ ሕዝብ አባላት መሆናቸውን፣ሁሉም ያንኑ አንድ አምላክ እንደሚያመልኩና ሁሉም ወደዚያው አንድ ስፍራ እንደሚወጡ የሚገልጽ ምስክርነታቸው ነበረ።

አሁን በአዲሱ ኪዳን የጌታን ስም የተሸከመው ኢየሱስ ነው፤ የእግዚአብሔርም ሕዝብ ለጌታ ስም ምስጋና ለማቅረብ አብረው በሚሰበሰቡበት ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የተዋጁ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ለዓለም ምስክርነት ይሰጣሉ። ቅዱስ ቃሉ መሰብሰባችንን እንዳንተው ያስጠነቅቀናል። ለጌታችን ስም ምስጋና ለማቅረብ እና ለማምለክ በአንድነት ስለምንሰበሰብ፣ ወንድማማቾች መሆናችንን እና የአንድ ሃገር ሕዝብ አባላት መሆናችንን ለዓለም ማሳወቃችን አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር በወሰነው ስፍራ፣ በኢየሱስ ስም እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ በአንድነት እንሰበሰባለን።