ዴሪክ ፕሪንስ ነኝ፤ ከቃሉ ለእናንተ የሚሆን መልዕክት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ።

አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት።በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው። መዝሙር 143:11-13

ያ በመንፈስ የተቃኘ የመዝሙረኛው ጸሎት፣እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሚመልስልን ለማመን የሚያስችሉንን ሦስት ግሩም ምክንያቶች ይሰጠናል። እነዚህ ሦስት ምክንያቶች ከማንኛውም የተለየ ሁኔታ ወይም አጋጣሚ፣ወይም ደግሞ ከሚሰማን ማንኛውም ዓይነት ስሜት ጋር የማይገናኙ ናቸው።

የመጀመሪያው ምክንያት፦ “ስለ ስምህ ስትል” የሚለው ነው። በኢየሱስ ስም ወደ ጌታ እንጸልያለን፤ እግዚአብሔርም ስለዚያ ስም ሲል ይመልሳል። የመጀመሪያው ምክንያት ይህ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት፡ “በጽድቅህ ነፍሴን ከመከራ አድናት” የሚለው ነው። ወደ እግዚአብሔር የምንጸልየው በራሳችን ጽድቅ ላይ ተመስርተን ሳይሆን፣ በኢየሱስ በኩል በእምነት በተቀበልነው በእርሱ ጽድቅ ላይ ተመስርተን ነው።

ሦስተኛውም ምክንያት፦ “በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው” የሚለው ነው። “ምሕረት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ትርጉሙ “የእግዚአብሔር ቃልኪዳኑን የመጠበቅ ታማኝነቱ” ማለት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በታማኝነቱ ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል። እኛ ታማኝ እንዳልሆንንና የማይገባን እንደሆንን በሚሰማን ጊዜ እንኳ፣እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን የመጠበቅ ታማኝነቱ ከቶ አይለወጥም።

ስለዚህ ሦስት ምክንያቶች አሉ፦ ስለ ስሙ፣ስለ ጽድቁ፣ እና ቃል ኪዳኑን ለመጠበቅ ታማኝ ስለሆነ። ጠላት እንዲያሸንፋችሁ አትፍቀዱ፤በራሳችሁ ጽድቅ መሠረት ላይ እንዲያቆማችሁ አትፍቀዱ፣ ምክንያቱም ያ ሊደግፋችሁ አይችልምና። ነገር ግን በእነዚህ መሠረቶች ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፦ በጌታ ስም፣ በጽድቁ፣ እና ቃል ኪዳኑን በሚጠብቅ ታማኝነቱ።